Saturday, August 17, 2013

ልጄ ልመርቅህ

ልጁ አባቱን በታላቅ ፍቅርና አክብሮት ያስታምማቸዋል፡፡ አባቱም ይህችን ዓለም የሚሰናበቱበት ጊዜ ሲደርስ ልጃቸውን በምርቃት ሊያከብሩት፣ በእግዚአብሔር እጅ ዋጋ ሊሰፍሩለት ፈለጉ፡፡ “ልጄ ልመርቅህ ነውና ምርቃቴን ተቀበል አሉት” እርሱም የአባትን ክብር ቀድሞ ያወቀ በመሆኑ የምርቃትንም ጥቅም ያውቃልና በጉልበቱ ተንበረከከ፣ እጁን ወደ ላይ ዘረጋ፣ ምርቃቱ መሬት ላይ ሳይነጥብ ሊቀበል ተሰናዳ፡፡ “አሜን ካለ ማለት በረከት ይቀራልና” አሜን ለማለት ተዘጋጀ፡፡ እኒያ አባትም ከአልጋቸው ዘቅዘቅ አሉ፣ እጃቸውን በልጃቸው ራስ ላይ አሳረፉ፡፡ ለዚያ የልጅ አባት፣ ለዚያ ወንድም ሴትም ሆኖ ለረዳቸው ሎሌ፣ ለዚያ በስም ብቻ ሳይሆን በተግባር ልጅ ለሆነው፣ ለዚያ የሕጻን ሽማግሌ፣ ለዚያ ልጄ ወዳጄ ለሚባለው ብላቴና የሚሰጡት የራሳቸው ነገር የላቸውም፣ ቢኖራቸውም ያንስባቸዋል፡፡ የልጃቸውን ፍቅርና ውለታ መክፈል የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ የእኔ እጅ ትንሽ፣ ደግሞም ቀዳዳ ነው፣ በሰፊው እጅ፣ ደግሞም በማያፈሰው በአምላኬ እጅ ልስፈርልህ፣ እኔ እመርቃለሁ፣ እርሱ ያትረፈርፍልሃል በሚል እምነት ለዘመናት ያሰቡትን ምርቃት በአጭር ቃል አዘነቡለት፡፡

ምርቃት የትልቅ ደስታ መግለጫ፣ የትልቅ ተቀባይነት ማረጋገጫ፣ የትልቅ በረከት ማመንጫ፣ የትልቅ ባላጋራ መፍጫ ነው፡፡ ሰው በአንደበቱ ሲመርቅ እግዚአብሔር ማኅተም ያሳርፋል፡፡ ይችን ዓለም የሚሰናበቱት እኒያ አባት የቀሪው ስንቅ ምርቃት ነውና ሊመርቁ ተሰናዱ፡፡ “ልጄ ወዳጄ ሆይ! የአንበጣ ሆድ፣ የጕንዳን ጉልበት፣ የሴት ብልሃት ይስጥህ” አሉት፡፡ ወዲያውም ከዚህች ዓለም ተሰናበቱ፡፡ ያ ልጅ ግን አባቱ የረገሙት መስሎት አዘነ፡፡ “አባቴ ቢያዝኑብኝ እንጂ የአንበጣ ሆድ፣ የጕንዳን ጉልበት ምንድነው? ሴትስ ምን ብልሃት አላት?” ብሎ አገር ለቆ ተሰደደ፡፡

በመንገድም ደክሞት በትካዜ ቊጭ ብሎ ሳለ አንድ ጥበበኛ ሽማግሌ የዛፉን ጥላ ፈልገው አጠገቡ አረፍ አሉ፡፡ ሽማግሌውም ወደዚህ ወጣት ዘወር ብለው፡- “ልጄ ምን ሆነሃል? ያዘንህ ትመስላለህ?” አሉት፡፡ እርሱም የሆዱን ይነግራቸው ጀመረ፡- “አባቴን በጣም አከብራቸው ነበር፤ ውርስን ስላስብ ምርቃትን ብዬ አስታመምኳቸው እርሳቸው ግን አዝነውኝ ኖሮ ረገሙኝ፡፡ የአንበጣ ሆድ የጕንዳን ጉልበት፣ የሴት ብልሃት ይስጥህ አሉኝ” በማለት ሀዘኑን ገለጠ፡፡ ሽማግሌውም ጥበበኛ ነበሩና ሳቅ ብለው፡- “አይ ልጄ አለማወቅህ እንጂ የመረቁህስ ምርቃት ትልቅ ምርቃት ነው” አሉት፡፡ እርሱም ዓይኑን አፍጥጦ፡- “የአንበጣ ሆድ፣ የጕንዳን ጉልበት ምንድነው? ሴትስ ምን ብልሃት አላት?” አላቸው፡፡

አረጋዊውም ይተረጕሙለት ጀመረ፡፡ “አንበጣ አሁን የለም ላሳይህ አልችልም፡፡ የአንበጣ ሆድ ይስጥህ ማለት አንበጣ የበላው ሁሉ ይስማማዋል፣ አንድ ቦታ ሰፍሮ ከተነሣ ቦታው በደቂቃ ባዶ ይሆናል፤ ስለዚህ የበላኸው ሁሉ ይስማማህ ማለት ነው፡፡ የጕንዳንን ጉልበትና የሴትን ብልሃት ግን አሳይሃለሁ” አሉት፡፡ ወደ መሬትም ጎንበስ ብለው አንድ ጕንዳን እርሱን የሚያህለውን ጓደኛውን ተሸክሞት ሲሄድ አሳዩትና፡- “የጕንዳን ጉልበት ይስጥህ ማለት የሰው ጠባይ አይክበድህ ማለት ነው” አሉት፡፡ እርሱም፡- “የሴትስ ብልሃት ምንድነው?” አላቸው፡፡ “ቆይ ታገሥ አሳይሃለሁ” ብለውት ይዘውት መጓዝ ጀመሩ፡፡ ወደ አንዲት ሴት ቤትም ገቡ፡፡ ያቺ ሴትም፡- “ቤት የእግዚአብሔር ነው” ብላ ተቀበለቻቸው፡፡ ሽማግሌውም ለዚህ ልጅ ያስጠኑት ጀመር፡- “አሁን የእግር ውሃ አቅርባልናለች፣ ቀጥሎ ጠላውን ከነዕቃው ልታመጣ ስትል ቆይ እርሱ ያግዝሽ ብዬ እልክሃለሁ፡፡ እርሷም ልታነሣ ጎንበስ ስትል ቆንጥጣት፣ ስትጮህ ምንድነው? እላለሁ፣ ያን ጊዜ የምትለውን ትሰማለህ” አሉት፡፡ በጥንቱ በየዕለቱ የሚከፈት ጠላ አለ፡፡ የአቦ፣ የሥላሴ፣ የሚካኤል ተብሎ ተመርጎ በገች ይደረደራል፡፡ ይህ ገች ከጋን መለስ ከእንስራ ከፍ የሚል ነው፡፡ ጠላውም በዕለቱ ታቦት ስም ለመጣው እንግዳ ፊት ለፊቱ ቀርቦ ይከፈትለታል፡፡ በዘመናዊው ዓለም ውስኪ እንደ ማውረድ ነው፡፡

እርሷም ልታመጣ ስትገባ ሽማግሌው፡- “ልጅ ነው እርሱ ያግዝሽ” አሏት፡፡ ልጁም ተከትሏት ገባ፡፡ ገቹንም ልታነሣ ጎንበስ ስትል ቆነጠጣት፡፡ በዚህ ጊዜ ጮኸች፡፡ ሽማግሌውም ከመቀመጫቸው ሳይነሡ “ምንድነው ልምጣ እንዴ?” ሲሉ “አይ አባቴ የአቦን ገች አነሣለሁ ብሎ የሥላሴን ገች አነሣው” አለቻቸው፡፡ ያም ልጅ ለካ የሴት ብልሃት ይህ ነው አለ፡፡ አባቱም ትልቅ ምርቃት እንደ መረቁት ተሰምቶት ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡

ሰው ዕድሜው እየገፋ ሲሄድ አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ ጫናዎች ያድሩበታል፡፡ አካላዊ ጫና የምንለው ጉልበቱ ይከዳዋል፣ ሮጦ መድረስ፣ ታግሎ መጣል፣ ወድቆ መነሣት ያቅተዋል፡፡ ስሜታዊ ጫና በሕይወት ዘመኑ ከሆነለት ያልሆነለት እየበዛ ይበሳጫል፡፡ የሚያውቁት ሰዎች በሞት በማለፋቸው፣ ስለ ድሮ መልኩና ጕብዝናው ሲያወራ የሚያረጋግጥለትና የሚያምነው ሰው በማጣት ያዝናል፡፡ መንፈሳዊው ጫና የፈጸማቸው ስህተቱ ድቅን ይሉበታል፡፡ የማያድጉ መስሎት የጣላቸው ልጆች አድገው ይቅር ቢሉት እንኳ ሕሊናው ይወቀሳል፡፡ አእምሮአዊ ጫናው እንኳን አዲስ ነገር ሊያውቅ ያወቀውም ይጠፋዋል፡፡ ሁኔታዎችን፣ ሰዎችን ይረሳል፡፡ እነዚህ ጫናዎች ለብስጭትና ለስካር እየጋበዙት ይመጣሉ፡፡ በሽታም ቀድሞ ማድረግ የሚችለውን ነገር እንዳያደርግ፣ የሚወደውን ምግብ እንዳይበላ ያደርገዋል፣ የሚጠላው ያ በሰው እጅ መውደቅ በግድ ይመጣበታል፡፡ ይፈልጉት የነበሩ ልጆቹ፣ ወደ ሥራ ሲሄድ ያለቅሱ የነበሩት ሕጻናት ዛሬ እርሱ በተራው ቢፈልጋቸውም አልገኝ ይሉታል፡፡ እነዚያ አቅፈውት አልላቀቅ የሚሉት ልጆች አሁን ለሠራተኛ ጥለውት በሩቅ ሲያዩት ስሜቱ መጎዳት ይጀምራል፡፡ ሽምግልናቸውን ተቀብለው የሚደሰቱ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ እየቆጠሩ ተመስገን የሚሉ ከሺህ አንድ ቢገኙ ነው፡፡

በሽምግልና ወራት ከማንም በላይ የማጽናናት አቅም ያላቸው ልጆች ናቸው፡፡ ልጆች ወላጆቻቸውን በማስተማር መንፈስ ሳይሆን በማስረዳት፣ በመከራከር ሳይሆን ሲጨርሱ በመናገር፣ በመውቀስ ሳይሆን ያለፈውን በማስረሳት ሊረዷቸው ይገባል፡፡ ከእኛ አንጻር እያየነው ሰባና ሰማንያ ዓመት ስለ ኖሩ በቃቸው ልንል አይገባም፡፡ ሰባና ሰማንያ ዓመት ንጹሕ የደስታ ዓመታት ሳይሆኑ ትግላቸው የበዛ ደስታቸው ያነሰ ዓመታት ናቸው፡፡ እነዚህን አረጋውያንን መንከባከብ ልዩ የመንፈስ ደስታ አለው፡፡ እግዚአብሔር ደስታችንን የሰለጠኑ ከተሞች ላይ አልደበቀውም፣ ወይም ባለጠግነት ውስጥ አላስቀመጠውም፡፡ ትዳር ውስጥም አልተደበቀም፡፡ ደስታችን የተቀመጠው በሌሎች ጉድለት ውስጥ ነው፡፡ የደካሞችን ጉድለት ስንሞላ የእኛም የደስታ ሸለቆ ይሞላል፡፡

እግዚአብሔር አንደበታችንን የፈጠረው እርሱን እንድናመሰግንበትና ሰዎችን እንድንመርቅበት ነው፡፡ ምርቃት የመልካም ምኞት መግለጫ አይደለም፣ ምርቃት የእምነት ስጦታ ነው፡፡ አንደበታችን ለተፈጠረበት ዓለማ ሲውል እግዚአብሔርም ደስ ይለዋል፡፡ እንድንራገም፣ ያጥፋው ይደምስሰው እንድንል አንደበታችን አልተፈጠረም፡፡ እኛ ስንመርቅ እግዚአብሔር መስፈር ይጀምራል፡፡ የሚጠሉንና የሚያስጨንቁንን እንኳ ስንመርቅ እኛን የመውደድ ጸጋ ይጨመርላቸዋል፡፡ በትክክል እንዲያዩን ዓይንን የሚያበራ ስጦታ ይመጣላቸዋል፡፡ የሚያጠላላን አንዱ አለመተዋወቅ ነውና፡፡

የበላነው ሁሉ ከተስማማን ትልቅ በረከት ነው፡፡ ሰጥቶአቸው ወይም ታመው መብላት ስለተሳናቸው ወገኖች መጸለይ ይገባል፡፡ አንዳንዶች ያገኙትን መብላት የማይችሉ፣ በሆዳቸው ሲሰደዱ የሚኖሩ፣ ትዳራቸውንም የሚፈቱ ናቸው፡፡ ሰው ሊያመልክ የሚገባው ሆዱን ሳይሆን እግዚአብሔርን ብቻ ነው፡፡ ሆድ ጣኦት ሲሆን ይጥላል፡፡ ልዑል ራስ ካሣ ኃይሉ፡- “የዕለት እንጀራችንን ስጠን ብለህ ከጸለይህ በኋላ የጠላ ቂጣ ቢሰጥህም ተመስገን ብለህ ብላ ሊታዘብህ ነውና” ብለዋል፡፡ ይህንንም ያጡ እንዳሉ እያሰብን የተሰጠንን በምስጋና ልንመገብ ይገባናል፡፡ መብልን የሚያጣፍጠው ትልቁ ቅመም ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር የበሉት ደረቅ እንጀራ ሲታወስ ይኖራል፡፡

የምንኖረው ከሰዎች ጋር ነው፡፡ ከሰዎች ጋር መኖራችን አማራጭ የሌለው ግዳጃችን ሳይሆን እግዚአብሔር የሰጠን ትልቅ በረከት ነው፡፡ ሰዎች ያስፈልጉናል፣ እኛም ለሰዎች እናስፈልጋቸዋለን፡፡ ደስታውም ሆነ ሀዘኑ ያለ ሰው ከባድ ነው፡፡ በመኖር ሂደት ውስጥ በሰዎች ብዙ የተጐዳን ብንሆን እንኳን ሰው ከነክፋቱ መልካም ነው፡፡ በጐዳና ብንወድቅ ከበው ደረት የሚመቱልን፣ ያምሃል ወይ? ብለው ጠጋ ብለው የሚጠይቁን፣ ስኳር በሽታ ቢኖርበት ነው ብለው አፋችንን ፈልቅቀው ስኳር የሚያቅሙን እነዚያ ሰዎች ያውም የማናውቃቸውና የማያውቁን ሰዎች ናቸው፡፡ ሰው መልካም ነው፡፡ መኪና የገጫቸውን ሰዎች ወጣቶቹ እንዴት አንሥተው ሕይወት ለማዳን ሲሯሯጡ ሳይ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፡፡ እኛ ዱርዬ የምላቸው ነገር ግን ርኅሩሆች የሆኑትን ወጣቶች ሳስብ ደስታ ይሰማኛል፡፡ መብላት ከእነዚህ ጋር ነው፡፡ እኩዮቻችን የሚጠየፉትን ሬሣችንን የሚሸከሙት እነዚህ ናቸው፡፡ ሰው መልካም ነው!

እኛ ሰው ያስፈለገን የጐደለን ነገር ስላለ ነው፡፡ ገንዘብ ብቻውን መልስ ሊሆንልን ስላልቻለ ዘበኛ ቀጠርን፣ የቤት ሠራተኛ አስገባን፡፡ ሰው ያስፈልገናል፡፡ ይህንን በደስታ ስንፈጽመው የሚመጡት ሰዎች ያስደስቱናል፡፡ ሰዎች የሚሆኑልን እንደ እምነታችን ነውና፡፡ “ሰው አጥፊዬ ነው” ያሉት ሁሉ በሰው ጠፍተዋል፡፡ “ደጅ ባድር ማን ይነካኛል? ሁሉ ዘመዴ ነው” ያሉ ሁሉም ዘመዳቸው ሆኗል፡፡ እግዚአብሔር ሲጠብቅ እንጂ ጠርጣራነት ከምንም አያድንም፡፡ እንደውም ከቀኑ በፊት መሞት ነው፡፡

ጉድለት ያለብን የሙያና የዕውቀት ብቻ አይደለም የምግባርና የጠባይም ጉድለት አለብን፡፡ ምክንያቱ ምንድነው? ስንል ሰው መሆናችን ነው፡፡ ሰው ቀዳዳ ስልቻ ነው፡፡ በአንዱ ሲሞላ በአንዱ ያፈስሳል፡፡ “የልጅ ነገር ሁለት ፍሬ፣ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” የተባለው ተረት “የሰው ነገር ሁለት ፍሬ፣ አንዱ ብስል አንዱ ጥሬ” ቢባል የተሻለ ነው፡፡ አዎ እነዚያም ወገኖቻችን ሰዎች ናቸውና እኛ ያለብን የሙያ፣ የዕውቀት፣ የምግባርና የጠባይ ጉድለት አለባቸው፡፡ ሰው ሆነን ያውም ተሸክመነው እየዞርን በሰው ድካም መገረም የለብንም፡፡ አንድ፣ አንድ እግር ያላቸው ቢተቃቀፉ ባለ ሁለት እግር ይሆናሉ፡፡ ስንቀራረብም እንሟላለን፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን አንበጣን፣ ጕንዳንና ልባም ሴትን በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ያነሣቸዋል፡፡ አንድ ሰው ሲነግሩኝ ከመዝሙረ ዳዊት 5 ምዕራፍ፣ ከመጽሐፈ ምሳሌ አንድ ምዕራፍ በየዕለቱ በማንበብ ወር ላይ ሁለቱንም መጻሕፍት ይጨርሳሉ፡፡ እኚህ ሰው፡- “መዝሙረ ዳዊት ከእግዚአብሔር ጋር ላለኝ ግንኙነት፣ መጽሐፈ ምሳሌ ከሰዎች ጋር ላለኝ ግንኙነት መጠበቂያ ነው” ብለዋል፡፡ አዎ ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ጥበቃ ያስፈልገዋል፡፡ ፍቅር አረም አይደለም፣ ካልተንከባከቡት አያድግም፡፡
የዳዊት ልጅ ሰሎሞን፡- “በምድር ላይ አራት ጥቃቅን ፍጥረቶች አሉ፤ እነርሱ ግን እጅግ ጠቢባን ናቸው፤ ገብረ ጕንዳንኃይል የሌላቸው ሕዝቦች ናቸው÷ ነገር ግን በበጋ መኖዋቸውን ይሰበስባሉ፡፡ ሽኮኮዎች ያልበረቱ ሕዝቦች ናቸው÷ ቤታቸውንግን በቋጥኝ ድንጋይ ውስጥ ያደርጋሉ፡፡ አንበጣዎች ንጉሥ የላቸውም÷ ሁላቸው ግን በመልካም ሥርዓት ይሄዳሉ፡፡ እንሽላሊትበእጅ ይያዛል÷ በነገሥታት ግቢ ግን ይኖራል” ብሏል (ምሳ. 30÷24-28)፡፡ በምሳሌ 6÷6-8 ላይም፡- “አንተ ታካች÷ ወደገብረ ጕንዳን ሂድ÷ መንገድዋንም ተመልክተህ ጠቢብ ሁን፡፡ አለቃና አዛዥ ገዢም ሳይኖራት መብልዋንም በበጋ ታሰናዳለች÷ መኖዋንም በመከር ትሰበስባለች” በማለት ተላላውን ሰው ይቀሰቅሰዋል፡፡

ጕንዳን ደካማ ፍጥረት ቢሆንም ብልህ ፍጥረት ነው፡፡ በመከር ደስታና ስካር ስለሚበዛ ሁልጊዜ እንደዚህ የሚኖር ይመስላል፡፡ “በፋሲካ የተገዛች ባሪያ ሁልጊዜ ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ፡፡ ጕንዳን ግን በመከር ዘመን ለክረምት ይሰበስባል፡፡ ጎንበስ ስንል ከምንማራቸው ትምህርቶች አንዱን ጕንዳን ይዞታል፡፡ ጕንዳን ትጉ ነው፣ ያለ ዕረፍትም ይሯሯጣል፣ ሁሉም የራሱን ድርሻ ይወጣል እንጂ አይተያዩም፤ የደከመም ካለ ይሸከሙታል እንጂ አውጥተው አይጥሉትም፡፡ የሚመለሰው ለሚሄደው መረጃ ይሰጠዋል፡፡ቆም ብለው መረጃ ተለዋውጠው ይተላለፋሉ፡፡ እየከለሱ ያሉት ገና ለሚጀምሩት ምናለ ትምህርት ቢሰጡ! ከጕንዳን አላንስም የሚል ቅንዓት የሚያድርብን መቼ ይሆን?

ጕንዳን ስፍራውን አይለቅም፣ ሰልፉንም አይስትም፣ በመነሻውና በውጊያው መካከል መንገዱ ነጻ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡ ሰውንም ሆነ እንስሳን የሚያሸንፍበትን ቦታ እስኪያገኝ አይነክስም፡፡ በውጊያ ሥርዓት፣ መስመርን ባለመልቀቅ ይጓዛል፡፡ በዚህም አንበሳን ሳይቀር ያሸንፋል፡፡ ኑሮው ግን መሣሪያን ይዞ እንደ መገንባት ያለ ነው፡፡ “በአንድ እጃችን ጠመንጃ በአንድ እጃችን ማጭድ” እንደ ተባለው፡፡

እኛ ከጕንዳን ይልቅ በንብ እንመሰጣለን፡፡ የሚጣፍጥ ነገር ስለምንወድ ነው፡፡ ንብ ሁለት ዓይነት ባሕርይ ያላት ይመስለኝ ነበር፡፡ ታታሪነትና መሸካከም፡፡ አንዱ ባንዱ ላይ ተደራርቦ ሲቀመጥ ከበደኝ የሚል ድምፅ አይሰማም፡፡ ነገር ግን በንብ ዓለም አንዱ አባል ሊኖር የሚችለው ከሠራ ብቻ ነው፡፡ ሲደክም አውጥተው ይጥሉታል፣ ይገድሉታል፡፡ ይህን የንብ መቻቻል የሚቻቻሉ ሰዎች ዛሬም አሉ፡፡ ሲደክም ግን አውጥተው ይጥላሉ፡፡ ለዚህ ነው፡- “ካለህ አለህ፣ ከሌለህ የለህም” የሚባለው፡፡ አንድ ሰው ስለ ፈረንጅ አገር ኑሮ ሲናገር፡- “ፈረንጅ አገር መኖር ማለት ሳይክል ላይ እንደ መውጣት ነው፣ ሳይክል እስከ ሄደ አትወድቅም፣ ስትቆም ግን ትወድቃለህ” ብሏል፡፡ አዎ በኑሮም ውስጥ እስከ ሠራና እስከ ሰጠ ድረስ የሚወደድ ልጅ፣ ባል፣ ጓደኛ … አለ፡፡ የዓለም ፍቅር “ከእንካ” ጋር ነው፡፡ በንብ ዓለም እጅግ በመጨከን የደከመውን፣ ጡረታውን ሳያስቡ አውጥተው ይጥሉታል፣ ነክሰው ይገድሉታል፡፡ የንብ ዕድሜ ግን ለዐርባ ቀን ነው፡፡ ለዐርባ ቀን እንዲህ መጨካከን ይገርማል! የእኛም ዘመን ጥቂት ነው፡፡ ግን የደከመውን የሚሸከም ማንነት የለንም፡፡ ነብር ጨካኝ ነው፣ ዋሽንት ከሰማ ግን እረኛውን ይጠጋዋል፡፡ በተመስጦም ይጠፋል፡፡ የዋሽንቱ ድምፅ ሲቆም ግን በጥፍሩ ይቧጭረዋል፣ ምናልባት አንድ ኪሎ ሥጋ እያነሣለት ነው፡፡ እስከ ተነፋለት ድረስ ነብር አይበላም፣ ሲቆም ግን ይበላል፡፡ ከነብር የላቀ ፍቅር እግዚአብሔር ያድለን!

“የጕንዳን ጉልበት ይስጥህ” ጕንዳን ሌላ ነገር መሸከም ባይችል እርሱን የሚመስለውን ጓደኛውን ግን መሸከም ይችላል፡፡ ጓደኛው በመንገድ ሲቀር ጥሎት አይሄድም ከሥሩ ገብቶ ተሸክሞት ይሄዳል፡፡ በጕንዳን ዓለም ያለው ፍቅር እስከ ሠሩ ድረስ ብቻ አይደለም፣ ሲደክሙም ለደካማ የሚሆን ጉልበት አለ፡፡ ትልቅ ጉልበት ጓደኛን መሸከም ነው፡፡ መሸከም እንጂ መጣል ጉልበት አይጠይቅም፡፡ በመንገድ ላይ የስምንት ዓመት ልጅ የሚሆን የስድስት ዓመት የሚሆነውን ወንድሙን አዝሎት ሳይ አሳዘነኝና፡- “ማሙሽ አይከብድህም ወይ? ለምን አታወርደውም?” አልኩት፡፡ የሰማሁት መልስ ግን እስካሁን የሚያስደነግጠኝ ነው፡፡ “ወንድሜ ስለሆነ አይከብደኝም!” ይህን ታሪክ የነገረኝ አንድ ወዳጄ ነው፡፡ አዎ ወንድም አይከብድም፡፡

በዛሬው ዘመን ሰው የሰውን ጠባይ መሸከም አልቻለም፡፡ ስለዚህ በቶሎ እንጀራውን፣ ትዳሩንና ንብረቱን ያፈርሳል፡፡ ገና ካሁኑ በሰው ጠባይ እንዲህ ተማርረን በዕድሜአችን መጨረሻ እንዴት ያለን ሰዎች ልንሆን ነው? ሁሉም ሰው የብጉንጅ ቊስል እንደ ያዘው አትንኩኝ ባይ ሆኗል፡፡ ፍቅራችን አልቆ በመጠባበቅ ነው የምንኖረው፡፡ አፋፍ ላይ የቆመው ግንኙነታችን ትንሽ ቊጣና ወቀሳ ከተሰነዘረበት በቶሎ የሚወድቅ ነው፡፡ ትልቅ ጸጋ የሰውን ጠባይ መሸከም መቻል ነው፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስ የሮሜን መልእክት ሲጽፍ የክርስትናን ፍሬ ገልጿል፡፡ የክርስትናው ፍሬ ግላዊ ቅድስና፣ ታማኝ ዜግነትን፣ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚመለከት ነው፡፡ ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት የበረታው የደከመውን እንዳይንቅ፣ የደከመውም በበረታው እንዳይፈርድ ሲገልጽ ማንም የማንም ዕዳ ሳይሆን ሁላችንም የእግዚአብሔር ዕዳ መሆናችንን ገልጻል፡፡ በክርስትናው መበርታታችን የሚለካው ገፍተን በመሄዳችን ሳይሆን ሌሎችን ለመሸከም ትከሻችንን በማስፋታችን ነው /ሮሜ. 14÷13/፡፡

ፊት የምናነሣው ሃምሳ ኪሎ አሁን ካቃተን ሃምሳ ኪሎው ሳይሆን እኛ ተለውጠናል ማለት ነው፡፡ የእኛ አቅም ደክሟል፡፡ እንዲሁም የወንድማችንና የእህታችን ጠባይ ከከበደን የእነርሱ መባስ ሳይሆን እኛ መድከም ምልክት ነው፡፡
የጕንዳን ጉልበት ይስጥህ!

No comments:

Post a Comment